DigArticle

ጠንካራ እና ጤናማ የሆነ የሙያተኝነት ባህል በሌለበት ተቋም እና ስርዓት የህግ የበላይነት ሊኖር እንደማይችል ተገለፀ

Posted 267 days ago (መጋ. 17, 2023 ) by Teklu Elias     0 Comments

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የንቃተ ህግ ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት የዐቃቤ ህግ ሙያዊነትን (Professionalism) ለማጎልበት ያለመ የፓናል ውይይት መጋቢት 07 ቀን በኢንተር ሌግዤሪ ሆቴል ተካሂዷል

 

በውይይቱ የተቋሙ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች እንዲሁም የቡድን መሪዎች ተሳትፈዋል

 

ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ እንደገለፁት ጠንካራ እና ጤናማ የሆነ የሙያተኝነት ባህል በሌለበት ተቋም እና ስርዓት የህግ የበላይነት ሊኖር አይችልም፡፡ በሀገራችን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በተለያዩ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ እንዲሁም ውስጣዊ እና ውጫዊ ተግዳሮቶች አንፃር ሙያተኝነት በሚፈለገው ደረጃ ያልጎለበተበት አውድ ውስጥ እንገኛለን ያሉት ሚንስትሩ በተቋማችን እንደ ግብ ያስቀመጥናቸውን ጉዳዮች ለማሳካት ሙያተኝነትን ማሳደግ እና ማጎልበት ይገባናል ብለዋል፡፡

 

ሚንስትሩ አክለውም ሙያተኝነትን ለማጎልበት የሚደረግ ምክክር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በመጠቆም ይህ ውይይት በተቋማችን ውስጥ በዘላቂነት ሙያተኝነትን ለማሳደግ እና ለማጎልበት ትርጉም ያለው አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ በንግግራቸው አመላክተዋል ፡፡

 

በፓናል ውይይቱ የዐቃቤ ህግነት ተሞክሯቸውን ያቀረቡት ዶ/ር ራስሙስ በኢትዮጲያ ውስጥ በርካታ ተግዳሮቶች መኖራቸውን ገልፀው በእነዚህ ችግሮች ውስጥም ፍትሕ ሚኒስቴር ለሙያዊነት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት መሆኑ የሚበረታታ እንደሆነ ገልፀዋል ፡፡

 

በዶ/ር ራስሙስ የቀረበውን የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮ ተከትሎ በተቋሙ የቀድሞ አመራርና ዐቃቤ ህግ በነበሩት አቶ እሸቱ ወ/ሰማያት እና በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ረዳት ጠቅላይ ዐቃቤ ህግና የህግ ጉዳዮች ዓለም ዓቀፍ ትብብር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በሆኑት አቶ የሱፍ ጀማል ለውይይት መነሻ የሆኑ ተሞክሮዎች የተካተቱባቸው ሰነዶች ቀርበው ውይይቱ ተካሂዷል፡፡

 

ውይይቱን ሲመሩ የነበሩት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስቴር ዴኤታ ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው ሙያዊነትን ለማጎለበት የግል ትጋት መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን በመጠቆም የፍትህ ጉዳይ የዜጎችን መብት ከማስከበርና የህግ የበላይነትን ከማስጠበቅ ጋር የተቆራኘ በመሆኑ የፍትሕ ተቋማትን እና ሙያተኞችን በአግባቡ መስራት እና ማጠናከር ለሀገር ግንባታ አስፈላጊ ጉዳይ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡


No CommentsYou need to login to comment.