DigArticle

ከመላው ዓለም የተውጣጡ ተቋማት ተወካዮች እና ባለሙያዎች በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አማራጭ ሰነድ ላይ እየመከሩ ይገኛሉ

Posted 2 years 1 days ago (መጋ. 16, 2023 ) by Teklu Elias     0 Comments

ሀገራችን ያለፉትን በደሎች እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተከትሎ የተፈጠረውን ቁርሾ እና ቁስል ለማከም እና ለማድረቅ ያስችላል በሚል በዘርፉ የላቀ እውቀት እና ልምድ ያላቸው ምሁራንን በማሳተፍ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ጥናት ስራ ሲሰራ ቆይቶ ከአንድ ወር በፊት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አማራጭ ሰነድ ተዘጋጅቶ ለህዝብ ይፋ መደረጉ ይታወሳል፡፡

 

የካቲት 27 ቀን 2015 ዓ.ምም የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ክቡር አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የፍትሕ ሚኒስትሩ ክቡር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ እና ከፌዴራል እና ከክልል የተውጣጡ ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች በተገኙበት የምክክር መድረኩ በይፋ መጀመሩ ይታወሳል፡፡

 

መርሃ ግብሩ ቀጥሎ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት፣ የሲቪል ማህበራት እና የዴሞክራሲ ተቋማት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ የቀድሞ ልዩ ዐቃቤያነ ሕግ፣ ዳኞች እና እርቀ ሰላም ኮሚሽን አመራሮች በተለያዩ ቀናት በተዘጋጁ 4 መድረኮች አማካኝነት በሰነዱ ላይ እንዲመክሩ ተደርጓል፡፡

 

ዛሬ መጋቢት 7 ቀን 2015 ዓ.ም በራዲሰን ብሉ ሆቴል በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አማራጭ ሰነዱ ላይ በመካሄድ ላይ ባለው ከፍተኛ መድረክም ከመላው አለም የተውጣጡ በአለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ደረጃ በሽግግር ፍትሕ ዙሪያ የሚሰሩ ዓለም ዐቀፍ ተቋማት፣ ጥናት እና ምርምር ያደረጉ እና መጽሃፍ የጻፉ ታላላቅ ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል፡፡

 

መድረኩ ላይ ተገኝተው መርሃ ግብሩን በንግግራቸው የከፈቱት የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴዔታ ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው በመልዕክታቸው የኢትዮጵያ መንግስት ያለፉትን በደሎች እና የመብት ጥሰቶች በሽግግር ፍትሕ ሂደት መፍትሄ እንዲያገኙ ለማድረግ የፖሊሲ ዝግጅት ስራዎችን በመካሄድ እና የአማራጭ ሰነድ ዝግጅቱን በመከወን ሀገራዊ የምክክር መድረክ ማካሄድ መጀመሩ የኢትዮጵያ መንግሥት የሽግግር ፍትሕን በከፍተኛ ትኩረት ወደ ተግባር በመለወጥ ዘላቂ ሰላም፣ ዕርቅና ፍትሕን ለማስፈን ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

 

በዚህ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ አማራጭ ሰነድ ላይ ምክክር ለማድረግ በተዘጋጀው መድረክ ላይ ለመሳተፍ እና እውቀታችሁን እና ልምዶቻችሁን ለማካፈል ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያ በመምጣት እና የመድረኩ አካል በመሆን ላሳያችሁት ቁርጠኝነት ከፍ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለው ያሉት ሚኒስትር ዴዔታው ሰነዱም ሆነ መድረኮቹ የተለያዩ ሃሳቦች እና አስተያየቶች እንዲነሱ በሚያስችል እና የአካታችንት መርህን በተከተለ ሁኔታ መዘጋጀታቸው ለእውነተኛ እና ትርጉም ላለው ምክክር እና የተሟላ የሽግግር ፍትህ የፖሊሲ ማዕቀፍ ለመንደፍ የራሱን ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡

 

ሚኒስትር ዴዔታው አክለውም በፖሊሲ አማራጭ ሰነዱ ላይ ጥልቅ ምክክር ይደረግ ዘንድ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ማሳተፍ መቻላችንም የምክክር ሂደቱን ታማኝነት እና ህጋዊነትን የሚያሳድገው ከመሆኑም በላይ በቀጣይ በፖሊሲ ትግበራ ወቅትም የመንግስት ቁርጠኝነትን የሚያረጋግጥ እና በሂደቱ ስኬት ከህዝብ፣ ከተጎጂዎች እና ከተጎዱ ማህበረሰቦች ጋር በሚደረገው የምክክር ሂደት ላይም አዎንታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር እንገነዘባለን ሲሉ ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያን የሽግግር የፍትህ ውጥኖችን ለመምራት ባለፉት ዓመታት ለተዘጋጁት ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ መርሆዎች ከፍ ያለ ቦታ ሰጥተናል ያሉት አቶ አለምአንተ አግደው በዚህ ረገድ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ዝግጅት ከፍተኛ የባለሙያዎች ቡድን እ.ኤ.አ. በ2019 በአፍሪካ ህብረት መሪዎች እና መንግስታት የፀደቀውን የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ እና የተባበሩት መንግስታት በሽግግር ፍሕህ ዙሪያ ያወጣቸውን የሕግ ማዕቀፎች እና ሀገራት ያጋጠሟቸውን ችግሮች ከግምት በማስገባት በኢትዮጵያ ውስጥ አውድ-ተኮር የሆነ የሽግግር የፍትህ ፖሊሲ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ዘላቂ ሰላም፣ ፍትህ፣ እርቅ፣ ማህበራዊ ትስስር እና ፈውስ እንደሚያመቻች ከፍተኛ ጥረት በመደረግ ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡

 

የፖሊሲ ዝግጅቱን በገለልተኝነት የሚመራው የባለሙያዎች ቡድን ለኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ፣ የተቀናጀ እና አውድ-ተኮር የሽግግር የፍትህ ፖሊሲን የመንደፍ ስልጣን ተሰጥቶት የቅድመ ፖሊሲ ዝግጅት ስራውን አከናውኖ አሁን ወደ ምንገኝበት የምክክር ምዕራፍ ገብቷል ካሉ በኋላ ቡድኑ በኢትዮጵያ የሽግግር የፍትህ ውጥኖች ላይ ያካሄደውን ጥናት እስኪሰምር ድረስ የኢትዮጵያ መንግስት ቁርጠኝነቱን እንደሚቀጥል አጽንኦት ለመስጠት እወዳለሁ ሲሉ መልዕክታቸው አስተላልፈዋል።

 

የክቡር ሚኒስትር ዴዔታውን የመክፈቻ ንግግር ተከትሎ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አማራጭ ሰነዱ በባለሙያዎች ቡድኑ አባላት አማካኝነት ቀርቦ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል፡፡ መድረኩ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል፡፡






No Comments



You need to login to comment.