DigArticle

የኦሮሚያ ክልል የማህበረሰብ አቀፍ የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ፤ የባህላዊ ፍርድ ቤት ተሞክሮ ቀርቦ ውይይት ተካሄደ

Posted 273 days ago (መጋ. 11, 2023 ) by Teklu Elias     0 Comments

 

ዛሬ በተጠናቀቀው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር እና የክልል ፍትህ ቢሮዎች የጋራ መድረክ በማህበረሰብ ዓቀፍ የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የኦሮሚያ ክልል የባህላዊ ፍርድ ቤቶችን ሚና በተመለከተ የተገኙ ውጤቶችን እና እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችን የሚያሳይ የተሞክሮ ሪፖርት አቀረበ፡፡

 

ሪፖርቱን ያቀረቡት የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ጉዮ ዋሪዮ ሲሆኑ በኦሮሚያ ክልል ሁሉም ዞኖች ስር ባሉ ወረዳዎች በዓመት 187,126 ጉዳዮች ለማህበራዊ ፍርድ ቤቶች ቀርበው እንደነበር አንስተው በዚህ ምክንያት ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ጉዳዮችን በ5% መቀነስ እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡

 

ኃላፊው በገለጻቸው በባህላዊ ፍርድ ቤቶች የዳኝነት ስርዓት ከሳሽና ተከሳሽ አሸናፊና ተሸናፊ ሳይኖር ሁሉም አሸናፊ (win win) ሆነው ተግባብተውና ተስማምተው የሚለያዩ ከመሆኑም በላይ ምስክሮች በእውነት የሚምሉበት እና የሚመሰክሩበት በመሆኑ እውነትን ለማውጣት የተሻለ ስርዓት ነው ብለዋል፡፡

 

በባህላዊ ፍርድ ቤቶች የሚታዩ ጉዳዮች ከመደበኛው ፍርድ ቤት በተሻለ ፍጥነት እልባት የሚያገኙበት እና ባህልና ሀገር በቀል እውቀቶች የሚዳብሩበት ከመሆኑም በላይ የአካባቢን ብሎም የሀገርን ሰላም የማስጠበቅ ሚናቸው ጉልህ መሆኑን ሀላፊው ገልጸዋል፡፡

 

የባህላዊ ፍርድ ቤቶች ዳኞችና ፀሀፊዎች ያለ ደሞዝ አገልግሎቱን የሚሠጡ መሆኑ እና የሚሰጡት ፍርዶች አልፎ አልፎ ተፈጻሚ ያለመሆን ችግር በቀረበው የተሞክሮ ሪፖርት ላይ እንደተግዳሮት ተጠቅሷል፡፡

የሪፖርቱን መቅረብ ተከትሎ በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ በሆኑት በክቡር አቶ ፍቃዱ ጸጋ እና በጽሁፍ አቅራቢው አቶ ጉዮ ዋሪዮ እየተመራ ውይይት ተደርጓል፡፡

 

በተመሳሳይ በእለቱ በተካሄደ መርሀ ግብር በተባበሩት መንግስታት ከአደገኛ መድሀኒቶች እና ወንጀል መከላከል ጽ/ቤት የመጡት ወ/ሮ ሌሊሴ ተርፋሳ በሰው መነገድና ሰዎችን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን ለመመርመርና ለማስቀጣት የተዘጋጀው የአሰራር ስርዓት ሰነድ አቅርበው ውይይት ተካሂዷል፡፡






No Comments



You need to login to comment.