Posted 1 years 321 days ago (መጋ. 10, 2023 ) by Teklu Elias 0 Comments
|
|
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ የኢትዮጵያ የፍትህ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን (መሰረታዊ ለውጥ) በሚል የተዘጋጀውን የመነሻ ጹሁፍ አዳማ ከተማ እየተካሄደ ባለው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር እና የክልል ፍትህ ቢሮዎች የጋራ መድረክ ላይ አቀረቡ፡፡
ባለፉት ጊዜያት የኢትዮጵያን የፍትህ ዘርፍ ለማሻሻል የተለያዩ የማሻሻያ ስራዎች የተሰሩ ቢሆንም ዜጎች ከፍትህ ዘርፉ የሚጠብቋቸውን መልካም ውጤቶች በበቂ ሁኔታ ማምጣት አልተቻለም፤ በመሆኑም አሁንም የፍትህ ዘርፉ ፍትህን በሚያሰፍንበት ሂደት እና በውጤቱ ላይ ከህብረተሰቡ የሚሰሙ እሮሮዎች በፍትህ ዘርፉ ላይ ያለውን የአመኔታ እና የእርካታ እጦት የሚያመላክቱ ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ ይህ ዘርፍ ከህብረተሰቡ የሚጠበቅበትን ውጤት ለማምጣት በሚያስችለው ልክ የማደስ ስራ እጅግ አድካሚ እና ፈታኝ ተልዕኮ ቢሆንም ይህ መነሻ ጽሁፍም የፖሊሲ አመንጪዎች እና የፍትህ ዘርፉ ተዋንያን በዘርፉ ሊመጡ ስለሚገባቸው የማሻሻያ ስራዎች ውቅራዊ አቅጣጫን ለማመላከት ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ክቡር ሚኒስትሩ ባቀረቡት የመነሻ ጹሁፍ ላይ ተመላክቷል፡፡
በክቡር ሚኒስትሩ የቀረበው ይህ መነሻ ጽሁፍ በአራት ዋና ዋና ክፍሎች የተዋቀረ ሲሆን በመጀመሪያው ክፍል ባለፉት አስርት አመታት በፍትህ ዘርፉ ላይ የተደረጉ ዋና ዋና የማሻሻያ ስራዎች በአጭሩ የተዳሰሰበት ክፍል ነው ።
በሁለተኛው እና በሶስተኛው ክፍል ደግሞ ከእነኚህ የማሻሻያ ስራዎች ሊወሰዱ የሚገባቸው ትምህርቶች የተዳሰሱ ሲሆን አጠቃላይ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ነባራዊ ከባቢ ዳሰሳ ተቃኝቶ ከእነኚህ አመላካቾች አንጻር በፍትህ ዘርፉ ሊደረግ የሚገባው የለውጥ እና ማሻሻያ ስራ በአዎንታዊ እና አሉታዊ ተጽዕኖዎቹ የሚመዘንበት ክፍል ነው።
የመነሻ ጹሁፉ በመጨረሻው እና በአራተኛው ክፍል ስር የፍትህ ዘርፉን በተመለከተ ሊወሰዱ የሚገባቸው የለውጥ እና የማሻሻያ እርምጃዎች አላማ፣ አካሄድ እና አግባብ ተተንትኖ በክቡር ሚኒስትሩ ቀርቧል፡፡
በቀረበው ሰፊ ሪፖርት ላይም በመድረኩ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፤ በቀጣይም እንደ ሀገር ይተገበራል ተብሎ ይጠበቃል ።
No Comments
You need to
login to comment.