DigArticle

ሚኒስቴር መሰሪያ ቤቱ በ2015 በጀት ዓመት የ6 ወር ዕቅድ አፈጻጸም ዙሪያ ግምገማ አካሄደ

Posted 1 years 253 days ago (ጥር 25, 2023 ) by Teklu Elias     0 Comments

ፍትሕ ሚኒስቴር ሕገ መንግስቱንና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን ከማክበርና ማስከበር፣ የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥ እንዲሁም የፌዴራል መንግስቱንና የሕዝብን የፍትሐ-ብሔር ጥቅም ከማስከበር አንፃር በ6 ወራት ውስጥ በርካታ ተግባራትን ስለማከናወኑ በትላንትናው ዕለት በተካሄደው የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ላይ ተበራርቷል፡፡

 

በመድረኩ የሚኒሰቴር መሰሪያ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች፣ የየሰራ ከፍል ኃላፊዎችና ቡድን መሪዎች የተገኙ ሲሆን የመንግስት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ፣ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ፣ የሃብት አስተዳደርና የህንፃ ግንባታ ፕሮጀክት የ6 ወር የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት በዝግጅትና በትግበራ ምዕራፍ ተከፍሎ በዝርዝር ቀርቧል፡፡

 

የመንግስት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ የ6 ወር አፈፃፀም ሪፖርት በፌዴራል ሕጎች ተፈጻሚነት ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ትብለጥ ቡሽራ የቀረበ ሲሆን በሪፖርቱም ተግባራትን በተቀመጠው ስታንዳርድ መሰረት መፈጸም፣ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችንና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በህግ ጥናት፣ በፍትሐ ብሔር ጉዳዮች፣ በንቃተ ህግና ስልጠና፣ በሴቶች፣ ህጻናትና ባለብዙ ዘርፍ ተግባራት፣ በትብብር ጥምረት፣ በሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሀ ግብርና ሌሎች በርካታ ስራዎች ዙሪያ የተጠናከረ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እድል የተፈጠረ ሲሆን የወንጀልና ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከል፣ ይቅርታና አመክሮ አፈጻጸም ክትትልና ውጤታማነት፣ የመንግስትና የህዝብን ፍትሐ-ብሄራዊ ጥቅም ማስከበር፣ በሕግ እና ፍትህ ጉዳዮች አለም አቀፍ ትብብር ማጠናከር፣ የሰብአዊ መብት ማክበር እና ማስከበር፣ የዜጎችን ንቃተ ሕግ ማሳደግ፣ የፌዴራል ሕጎች ተፈጻሚነትን ማጎልበት፣ የሕግ ጥናት፣ ማርቀቅና ምክር አፈጻጸም ማጠናከር እንዲሁም የወንጀል ሥነ-ሥርአት እና ማስረጃ ህግን ለማጸደቅ ትኩረት ተሰጥቶ የተሰራ ስለመሆኑ ተመላክቷል፡፡

 

በሌላ በኩል ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት አሰጣጥ ተደራሽነትን ማሻሻልል፣ የጥብቅና አስተዳደርና ክትትልን ማጠናከር፣ ለንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ የሚቀርቡ የይግባኝ ቅሬታዎች ውሳኔ አሰጣጥን ማሻሻል፣ በንግድ ውድድር፣ ሸማቾች መብትና በምርት ገበያ ዙሪያ ለዳኝነት ችሎቱ የሚቀርቡ ክሶች የውሳኔ አሰጣጥን ቀልጣፋ ማድረግ እንዲሁም ዘመናዊ አሰራርንና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራትም በተሻለ ደረጃ ስለመከናወናቸው በዘርፉ ሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

 

የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የ6 ወር የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት የዘርፉ ጽ/ቤት ኃላፊ በሆኑት በአቶ በረከት ማሞ አማካኝነት የቀረበ ሲሆን ዘርፉ የወንጀልና የወንጀል ስጋትን መቀነስ፣ የወንጀል ህግ አፈፃፀም ውጤታማነት የማሳደግና የምርመራ መዛግብትን የማጥራት ምጣኔ በሁሉም የወንጀል ዓይነቶች በአማካኝ 81. 83% የማድረስ፣ በ15480 መዛግብት ላይ የተለያዩ ውሳኔዎች የማሰጠት፣ የመርታት ምጣኔ በሁሉም የወንጀል ዓይነቶች በአማካይ 93.9% የማድረስ በዚህም በ673 ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነትና የቅጣት ውሳኔ ማሰጠት የተቻለ ሰለመሆኑ ተብራርቷል፡፡

 

በተጨማሪም በልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች፣ በሴቶችና ህፃናት በሚፈፀሙ ወንጀሎች፣ በምስክሮችና ተከሳሾች አለመቅረብ የሚቋጡ መዛግብት መቀነስ፣ ከሙስና፣ ከኢኮኖሚ እንዲሁም ከተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች አኳያ የተሸለ አፈጻጸም ማስመዝገብ የተቻለ ስለመሆኑ እንዲሁም የሕግ ኦዲትና ኢንስፔክሽን ሥራን ማጠናከር፣ በወንጀል የተገኘ ሃብትን ማስመለስ፣ የሰብዓዊ መብት የማክበርና የማስከበር አፈፃፀምን ማሻሻል፣ የወንጀል ምስክሮች፣ ጠቋሚዎች፣ ተጎጂዎች አገልግሎት አሰጣጥን ማሳደግ ስለመቻሉ በሪፖርቱ ተጠቅሷ፡፡

 

የተቋሙን የሀብት አስተዳደር አፈጻጸም በተመለከተ የሀብት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ የኋላሸት አግዝ ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን በተለይም አገልግሎትን ለማዘመን የኢ-ፔይመንት፣ የሲቪል ሰርቪስ የተቀናጀ የመረጃ ስርዓት አጠቃቀም፣ የኢ- ጂፕ፣ የውስጥ ትራንስፖርት ስምሪት ሲስተም የመዘርጋት፣ ከአሰራር ስርዓትና አደረጃጀት አንፃር 98% የሠራተኛ ምደባ የማካሄድ፣ የንብረት ማስወገድ እንዲሁም የተለያዩ የውስጥ አሠራር ጥናት ማድረግና የአሰራር ስርዓት የመቅረጽ ተግባራት ውጤት ማስመዝገብ ከተቻለባቸው ተግባራት መካከል ዋንኛዎቹ መሆናቸውን በቀረበው ሪፖርት ተመላክልቷ፡፡

 

በስተመጨረሻም ከተቋሙ የህንጻ ግንባታ ፕሮጀክት አፈጻጸም ጋር በተያያዘ የስትራቴጂክ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ መንግሰቴ ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያለዉን የቢሮ እጥረት ከመቅረፍና አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ህንጻዎችን ለሥራ ምቹ ከማድረግ አኳያ በተያዘው በጀት ዓመት 6 ወራት ውስጥ የዋናው መስሪያ ቤት እድሳትን ጨምሮ ለቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች አዲስ እየተገነቡ ያሉ ሕንፃዎች ተጠናቀው አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ ስራ ተከናውኗል ብለዋል፡፡

 

በቀረቡ ሪፖርቶች ዙሪያ ተሳታፊዎች ውይይት ያደረጉ ሲሆን በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት የታየዉን ዉጤታማ አፈጻጸም አጠናክሮ በማስቀጠል በተለይም ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለዉን ቅንጅታዊ አሰራር ማጎልበት እንዲሁም የፍትሕ ሥርዓቱን ይበልጥ ዉጤታማ የሚያደርጉ ስትራቴጂካዊ አሰራሮችን በመተግበር መንግስትና መላዉ ማህበረሰብ ከተቋሙ ማግኘት የሚገባቸዉን አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቸል የሚያስፈልግ መሆኑን በመገንዘብ በ6 ወራት ዉስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ያለተሳኩ ተግባራትን ጨምሮ በቀጣይ 6 ወራት ለማከናወን በዕቅድ የተያዙ ተግባራትን በሙሉ አቅም በመተግበር ለተሸለ ውጤታማነት መሥራት እንደሚያስፈልግ አቅጣጫ በመስጠት የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ መድረኩ ተጠናቋል፡፡






No Comments



You need to login to comment.