የኢፌዴሪ  ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሥልጣንና ተግባራት


በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 መሠረት ለተቋሙ የተሰጡ ስልጣን እና ተግባራት እንደሚከተለው ቀርቧል:-

1. የወንጀል ፍትህ ፖሊሲን የሚመለከታቸውን አካላት በማስተባበር ያዘጋጃል፤ ሲፀድቅም ተግባራዊነቱን ያስተባብራል፣ ይከታተላል፣ ያረጋግጣል፤

2. በሕግ ጉዳዮች የፌዴራል መንግስት ዋና አማካሪ እና ተወካይ ሆኖ ይሰራል፤

3. ወንጀል ጉዳይን በተመለከተ፦

/ በሌሎች ህጎች ለፖሊስ የተሰጠው ስልጣን እንደተጠበቀ ሆኖ በፌዴራል ፍርድ ቤት ስልጣን ስር የሚወድቅ የወንጀል ምርመራ እንዲጀመር ያደርጋል፣ ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል፣  

/  ምርመራው በሕግ መሰረት መከናወኑን ያረጋግጣል፣ አስፈላጊውን ትእዛዝ ይሰጣል፤

/  የተጠናቀቁ የምርመራ መዝገቦችን ከሕግና ከማስረጃ አንፃር መርምሮ ውሳኔ ይሰጣል፤

የጥፋተኝነት ድርድር ይወስናል፣ ድርድር ያደርጋል፣ አማራጭ የመፍትሄ እርምጃ እንዲወሰድ ይወስናል፣ ተግባራዊነቱን ይከታተላል፤

የፌዴራል መንግስትን በመወከል የወንጀል ጉዳዩች ክስ ይመሰርታል፣ ይከራከራል፣ ለህዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ክስ ያነሳል፣ የተነሳ ክስ እንዲቀጥል ያደርጋል።

/  ሀገራዊ ይዘት የሚኖረው ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩን በማማከር ክስ ስለሚያነሳበት አግባብ መመሪያ ያወጣል፤

/  ፍርድ ቤቶች በወንጀል ጉዳይ የሚሰጡዋቸው ውሳኔዎችና ትእዛዞች መፈፀምና መከበራቸውን ይከታተላል፣ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋል፤

በፍርድ ቤት የሚወሰኑ የወንጀል ቅጣቶች በአግባቡ እንዲፈፀሙ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥርዓቶችን ያደራጃል ወይም መደራጀታቸውን ያረጋግጣል፤

/ የሞት ቅጣት ውሳኔዎችን ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ያቀርባል፣ አፈፃፀሙን ይከታተላል።

4. የፍትሐ ብሔር ጉዳዮችን በተመለከተ፦

/ በፌዴራል የመንግስት መሥሪያ ቤቶች የሕዝብ እና የፌዴራል መንግስት መብትና ጥቅም ወኪል ሆኖ ይከራከራል፣ ያስከብራል፣ እንዲከበሩ ያደርጋል፣ ይከታተላል፣ ይቆጣጠራል፤

/ በግዙፍ የመንግስት ፕሮጀክቶች የውል ዝግጅት እና ድርድር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ያደርጋል፣ የሕዝብና የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶች ጥቅም ይጎዳል ብሎ ሲያምን በሌሎች ጉዳዮች ውል ዝግጅትና ድርድር ያደርጋል ወይም የሚመለከታቸውን አካላት ያማክራል፤

/ የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤትን በመወከል የፍትሐብሔር ክስ ይመሰርታል፤ በከሰሱበት ወይም በተከሰሱበት የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ላይ ክርክር ያደርጋል፤ በክርክር አመራር ላይ ለመሥሪያ ቤቶች አቅጣጫ ይሰጣል፣ በሕግ መሠረት ፍርድን ያስፈፅማል፤

/ የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶች እርስ በርሳቸው ያልተግባቡባቸው የፍትሐብሔር ጉዳዩች በፍርድ ቤት ወይም ከፍርድ ቤት ውጭ ባለ አማራጭ የክርክር መፍቻ መንገድ እንዲወሰን ውሳኔ ይሰጣል፣ በውሳኔው መሰረት መፈፀሙን ያረጋግጣል፤

/ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የፍትሐብሔር ክስ ለመመሥረት የገንዘብ አቅም የሌላቸውን ዜጎች በተለይም ሴቶችን፣ ሕፃናትን፣ አካል ጉዳተኞችን እና አረጋውያንን ወክሎ ይከራከራል፤

/ የገንዘብ አቅም የሌላቸው የወንጀል ተጎጂ የሆኑ ተበዳዩች እንዲካሱ መልሰው እንዲቋቋሙ እንዲሁም ከጉዳቱ የተያያዙ የፍትሐ ብሔር ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ እነሱን በመወከል የፍትሐብሔር ክስ ያቀርባል ወይም ይደራደራል፤

/ የኢፌዲሪ መንግስት በዓለምአቀፍ የዳኝነትና ከፊል ዳኝነት አካላት በሚከስበት ወይም በሚከሰስበት ጉዳይ መንግስትን በመወከል እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር ክርክር ያደርጋል፤ ድርድር ያካሂዳል፤ ውሳኔውንም ያስፈፅማል፤

5. የሕግ ማርቀቅ ሥራን በተመለከተ፦

/ በፌዴራል መንግሥት የሚወጡ ሕጎች የሕግ ረቂቅ ዝግጅት ይሰራል፤ የመንግስት አካላት የሚያዘጋጁት ረቂቅ ሕግ ከሕገ መንግስቱና ከፌዴራል ሕጎች ጋር የተጣጣመ መሆኑን ያረጋግጣል፣ ለሚመለከታቸው ክፍሎችም አስተያየት ያቀርባል፤ በክልሎች ጥያቄ ሲቀርብለት የሕግ ረቂቆችን በማዘጋጀት ይረዳል፤

/ የሕግ ማሻሻያ ጥናቶችን እንዲሁም የኮዲፊኬሽንና የፌዴራል ሕጐችን የማሰባሰብና ማጠቃለል ሥራ ይሰራል፤ የክልል ሕጎችን ያሰባስባል፣ እንደአስፈላጊነቱም እንዲጠቃለሉ ያደርጋል፤

/ ኢትዮጵያ የምትፈርመው ወይም የምትቀበለው ዓለም አቀፍ ስምምነት ሕገ መንግስቱን እና የአገሪቱን ሌሎች ሕግጋት ያገናዘበና ከብሔራዊ ጥቅም አንፃር ተቀባይነት ያለው መሆኑን ያረጋግጣል፤

6. የፌዴራል መንግስቱ ሕጐች ተግባራዊ መደረጋቸውን እና አተገባበራቸውም ወጥነት ያለው መሆኑን ያረጋግጣል፤ እንዲሁም አስፈፃሚ የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶች ሥራቸውን በሕግ መሰረት ማከናወናቸውን ያረጋግጣል፤

7. የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ለፌዴራል መንግስት ባለስልጣናት፣ ሹመኞች፣ ተመራጮች፣ ሰራተኞች እንዲሁም የግሉ ዘርፍ ተሳታፊዎች እንደየአስፈላጊነቱ የሕግ ሥልጠና ይሰጣል ወይም እንዲሰጥ ያደርጋል፤

8. ሰብአዊ መብትን በተመለከተ፦

/ ነፃ የሕግ ድጋፍን አሰጣጥ ስትራቴጂዎችን ይቀርፃል፣ አፈፃፀሙን ይከታተላል፣ በመስኩ የሚሰማሩ አካላትን ያስተባብራል፤

/ ብሔራዊ የሰብአዊ መብት የድርጊት መርሀ ግብርን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ያዘጋጃል፣ አፈፃፀሙን ይከታተላል፤ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚመለከታቸውን አካላት ያስተባብራል፣ ለሚመለከታቸው አካላት ሪፖርት ያቀርባል፤

/ በፖሊስ ጣቢያና በማረሚያ ቤት ቁጥጥር ሥር ያሉ ሰዎችን ይጎበኛል፣ አያያዛቸው እና ቆይታቸው በሕግ መሰረት መፈጸሙን ያረጋግጣል፣ ሕገ ወጥ ተግባር እንዲታረም እና እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋል፤

/ የሰብአዊ መብት ትምህርት እና የንቃተ ሕግ ለማዳበር በተለያዩ ዘዴዎች ትምህርት ይሰጣል፤ በዘርፉ የተሰማሩ የሚመለከታቸውን አካላት ያስተባብራል፤

/ ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸውን ወይም የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍና አህጉራዊ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች አፈፃፀማቸውን ይከታተላል፣ ለሚነሱ ጉዳዮች እንደ አግባብነታቸው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር ምላሽ ይሰጣል፤ የስምምነቶቹን ብሔራዊ የአፈፃፀም ሪፖርት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጃል፤

9. ስለ ሕግ ጥናትና ስልጠና፦

/ አሰራሩን ውጤታማ ለማድረግ ጥናትና ምርምር ያደርጋል፤

/ የወንጀል ፍትሕ መረጃዎችን መሰብሰብ፣ ማደራጀት፣ መተንተንና ማሰራጨት የሚያስችል ሥርዓት ይዘረጋል፣ ያስፈፅማል፤

/ ዐቃቤያነ ሕግ ስለ ስራቸው ያላቸውን አመለካከት፣ እውቀትና ክህሎት በተከታታይ እና በየደረጃው ለማሳደግ ሥልጠና ይሰጣል ወይም ስልጠና እና ትምህርት እንዲሰጣቸው ያደርጋል፤

10.የዐቃቤ ሕግ የውሳኔ አሰጣጥ እና የፍቅደ ሥልጣን አጠቃቀም ወጥነትን ለማረጋገጥ መመሪያ ያወጣል፣ ተግባራዊ መደረጉን ያረጋግጣል፤

11.በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ደረጃ የጥብቅና አገልግሎት ለሚሰጡ ጠበቆች በሕግ መሠረት ፈቃድ ይሰጣል፣ ያድሳል፣ ያግዳል፣ ይሰርዛል፤ ጠበቆችንና የጥብቅና አገልግሎትን ያስተዳድራል፣ ይቆጣጠራል፤

12.በፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስልጣንና ተግባር ስር የተመለከተው እንደተጠበቀ ሆኖ በወንጀልና ፍትሐብሔር ጉዳዩች ዓለም አቀፍ ግንኙነትና ትብብር ያደርጋል፤

13.በዐቃቤያነ ሕግ የሚሰጡ ውሳኔዎች በሕግ መሰረት መከናወናቸውን የሚያረጋግጥ የኢንስፔክሽን ክፍል ያደራጃል፣ ጉድለቶችን በጥናት አስደግፎ ይለያል፤ በግኝቱ መሠረትም እንዲታረሙ ያደርጋል፣ እርምጃ ይወስዳል ወይም እንዲወሰድ ያደርጋል፣ መልካም ተሞክሮዎችን ያስፋፋል፤

14.የንብረት ባለቤትና የይዞታ ባለመብት ይሆናል፣ ውል ይዋዋላል፣ በራሱ ስም ይከሳል፣ ይከሰሳል፤

15.የንብረት ባለቤትና የይዞታ ባለመብት ይሆናል፣ ውል ይዋዋላል፣ በራሱ ስም ይከሳል፣ ይከሰሳል፤

17.በሌሎች ህጎች የተሰጡትን ሥልጣንና ተግባራት ወይም ዓላማውን ለማስፈፀም የሚረዱ ሌሎች ተግባራትን ያከናውናል፡፡

በሌሎች ሕጎች ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተሰጠ ተግባርና ኃላፊነት

/ አዋጅ ቁጥር 1097/2012

1.ለሚኒስትሮች የተሰጠውን የወል ሥልጣንና ተግባር ሥራ ላይ ያውላል፤

2.ተጠሪ የተደረጉለትን አስፈፃሚ አካላት በበላይነት ይመራል፣ ያስተባባራል፣ አደረጃጀታቸውን የስራ ፕግራሞቻቻውን እና በጀታቸውን መርምሮ ለሚመለከተው እንዲቀርብ ያደርጋል፤

3.በፌደራል ፖሊስ ምርመራ ዘርፍ የሚከናወኑ የምርመራ ሥራዎችን በበላይነት ይመራል፣ ይቆጣጠራል፣ይከታተላል፣ ያስተባብራል፤

4.በምርመራ ሥራ ላይ ለተሰማሩ መርማሪዎችና ኃላፊዎችን የሥራ ስምሪት ይሰጣል፣ ይቆጣጠራል፤